About Us

መግብያ

ኢትዮዽያ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣የሳይንስና የባህል ድርጅት/UNESCO/ ባህረ መዝገብ ውስጥ ካስመዘገበቻቸው ቅርሶች ኣንዱ የሆነው የሐወልቶች መገኛ ኣክሱም ከተማ በዚሁ ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን የሃገራችን የጉዞ መስመርም /historic rout of Ethiopia/ በክልሉ የሚያልፍ ነው። በመሆኑም ክልሉ ኣለም ኣቀፍ የቱሪዝም መዳረሻ እንዲሆን ኣስችሎታል/ያስችለዋል።

የትግራይ ክልል የኢትዮዽያ ጥንታዊ  የስልጣኔ ምንጭ ከሆኑ ክልሎች በምሳሌነት ስሟ የሚጠራ ሲሆን የጥንታዊው ስልጣንያችንና  የታሪካችን ኣሻራ የሆኑ በርካታ ታሪካዊ ፣ባህላዊና ተፈጥራዊ ቅርሶች ይገኙባታል።

ከነዚህ ቅርሶች መካከል የኣክሱም ወጥ ሃወልቶች ፣ከኣክሱም ስልጣኔ  ጋር ተያያዥነት ያላቸው ኣብያተ መንግስቶችና መቃብሮች፣ቅድመ ልደተ ክርስቶስ በስምንተኛው ምዕተ ዓመት እንደተሰሩ የሚነገርላቸው ግራት ባዓል ግብሪና  ይሓ ቤተመቅደስ ፣ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያለው የቅርብ ግዜ ግኝት የሆነው ዓዲ ኣካውሕ ቤተ ሙክራብ፣የተለያዩ  ከዓለት የተፈለፈሉና ግንብ  ኪነ-ህንጻዊ ኣሰራራቸው፣ስነጥበባዊ ቅርፆቻቸው፣ጥንታዊ ስእሎቻቸው ፣ፅሑፎቻቸው፣የቦታኣቀማመጣቸው ማራኪ የሆኑ ከ4ኛው-15ኛው ክ/ዘመን የተገነቡ ኣብያተክርስትያንና  ገዳማት፣ስርወ ታሪኩ ከ7ኛው ክ/ዘመን የሚጀምረው የነጋሽ መስጊድ ዋነኞቹ የትግራይ ታሪካዊ መስህቦች ናቸው።

ትግራይ ከዘመን ዘመን ከትውልድ ወደ ትውልድ በቅብብሎሽ እየተሸጋገረ የመጣ፣  ሕብረተሰቧ የኣኗኗር ዜይቤውን፣የእርስበርስ ግንኝነቱንና ከሌሎች ጋር ያለው  መስተጋብር  የሚያንፀባርቅበትና የማንነቱ መገለጫ የሆኑ የሚኮራባቸው በባህላዊ መስህብነት የሚካተቱ የባህላዊ እሴቶች ባለቤትም ናት።ከነዚህም ውስጥ  ኣሸንዳ፣ መስቀልና ጥምቀት ያሉ ባህላዊ በዓላት በቱሪዝም መስህብነታቸው ይበልጥ የሚጠቀሱ ሲሆኑ  ሕዳር ፅዮን፣ሆሳእናና ዓሹራ  በመሳሰሉ  በድምቀት በሚከበሩ ባህላዊና ሃይማኖታዊ በዓላቶቿም ትታወቃለች።

ትግራይ ያላት መልክኣምድራዊ ኣቀማመጥ፣ኣገር በቀል የዕፅዋትና የእንስሳት ዝርያዎቿ፣ ወንዞቿ እንዲሁም አየር ንብረቷ በራሳቸው ተፈጥራዊ የቱሪዝም ሃብቶች  ናቸው።ከነዚህም ውስጥ በእሳተ ጎመራ እንደተፈጠሩ የሚነገርላቸው የጥቁር ኣፍሪካውያን   የነፃነት ተምሳሌት የሆኑት የዓድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች፣ከተደራረቡ ዓለቶች የተፈጠሩ የገርዓልታ ተራሮች፣ቃፍታ ሸራሮ ብሄራዊ ፓርከ በዋነኛነት የሚጠቀሱ ሲሆኑ ሌሎች እንደነ ተከዘ ፣ ሓሸንገ፣ሕጉምቡርዳ /ደን/፣ኣምባላጀና ግራ ካህሱ ተራሮች የመሳሰሉ ተፈጥራዊ መስህቦችም ይገኙባታል።

 በኣጠቃላይ  በክልሉ ሌሎች የማይንቀሳቀሱ ቅርሶችን ሳይጨምር 120 ገደማ የሚሆኑ ውቅር ኣብያተክርስትያንና ገዳማት፣3475 የሚጠጉ ግንብ ኣብያተክርስትያን እንዲሁም 6948 ገደማ የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽ ቅርሶች እንዳሉ ይታወቃል።

እስካሁን  እየተካሄዱ ባሉ የኣርኪኦሎጂ ቁፋሮ ጥናትና ምርምር`  በጅምር የተተዉ ቀጣይ ጥናትና ምርምር የሚያስፈልጋቸው ኣዳዲሰ ግኝቶች እየተገኙ እንደሆነና  ኣካባቢው ገና ሙሉ በሙሉ ያልተጠናና ወደፊት በሚደረጉ ጥልቅና ሰፋፊ ጥናቶችና ምርምሮች ሌሎች በርካታ የቅርስ ክምችቶች ሊገኙበት የሚችል እምቅ የቱሪዝም ሃብት እንደሆነ በዙርያው ጥናትና ምርምር ያካሄዱ ባለሞያዎች ይጠቁማሉ።

በ UNESCO ባህር መዝገብ ውስጥ ስሙ ሰፍሮ በቱሪዝም መስህብነት ዓለምኣቀፍ እውቅና ካገኘው የኣክሱም ሃወልት በተጨማሪ በዓለም ቅርስነት ተመዝግበው የክልሉንና የአገራችንን ስም ልያስጠሩ የሚችሉ በርካታ የቱሪዝም መስህቦች የሚገኙባት ናት።ከነዚህም ውስጥ ከቅርብ ግዜ ወዲህ የኣሸንዳን በዓል፣የይሓ ኣርኪኦሎጂካል ስፍራን፣የዓድዋ ተራሮችን፣የገርዓልታና የኣልነጃሺ ጥንታዊ ሓይማኖታዊ ስፍራዎችን በ UNESCO ለማስመዝገብ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ከ ፌደራል ቅርስ ጥበቃ ጋር በመሆን ከፍተኛ ጥረት በማደረግ ላይ ይገኛል።

የዚህ ፅሑፍ ዓላማም ትግራይ ያሏት ተፈጥራዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶች ለማስተዋወቅና እንዲጎበኙ ለማድረግ ሲሆን በተጨማሪም መስህቦቹን በፅሑፍ ሰንዶ በማኖር ለመጪው ትውልድ ለማቆየት ነው።በመሆኑም ከትግራይ መስህቦች መኣድ  ለቅምሻ ያክል ጥቂቶቹን በዚሁ መፅሃፍ ኣካትቶ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል/ተካተው ቀርበዋል።

 

ትግራይ ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ፣ባህላዊና ተፈጥራዊ የቱሪዝም ቅርሶችን  በፅሑፍ ሰንዶ ማኖር ለመጪው ትውልድ ማቆየት ከማስቻሉ በዘለለ መስህቦቹን ለኣገር ውስጥ ጎብኚዎች በማስተዋወቅ የኣገር ውስጥ ቱሪዝምን በማሳደግ ረገድ የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።በመሆኑም ከትግራይ መስህቦች መኣድ  ለቅምሻ ያክል ጥቂቶቹን በዚሁ መፅሃፍ ኣካትቶ እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል/ተካተው ቀርበዋል።